የመረጃ አያያዝ ስርዓትን በዘመናዊ መንገድ የሚያዘምን የዌብ ፖርታል ዌብ ሳይት ምረቃ ተካሄደ
የመረጃ አያያዝ ስርዓትን በዘመናዊ መንገድ የሚያዘምን የዌብ ፖርታል ዌብ ሳይት ምረቃ ተካሄደ
‎
‎ነሀሴ 9/2018 ዓም የሳንኩራ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ህ/ግንኙነት
‎
‎በስልጤ ዞን የሳንኩራ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት የመረጃ አያያዙን የሚያዘምን የዌብ ፖርታል ማስጀመሪያና በቴክኖሎጂው አጠቃቀም ዙሪያ ለባለድርሻ አካላት ስልጠና ሰጥቷል።
‎
‎ በመርሃ-ግብሩ ላዬ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የሳንኩራ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ዋና ኃላፊ አቶ አብዱልፈታ ሰልማን የዌብ ፖርታል ማበልፀጊያ ስራ ቀጣዩን የፓርቲውን የዘመናዊነት እና የተደራሽነት ጉዞ የሚያፋጥን ትልቅ እርምጃ ነው ብለዋል፡፡
‎
‎በዘመናዊው ዓለም ተቋማዊ አሰራርን ማዘመን ፣ መረጃን ለህዝብ ግልጽ እና ተደራሽ ማድረግ እንዲሁም ከአባላት እና ከደጋፊዎች ጋር የሚደረገውን ግንኙነት በቴክኖሎጂ የተደገፈ ማድረግ የህልውና ያህል አስፈላጊ ጉዳይ ስለመሆኑም አቶ አብዱልፈታ ተናግረዋል፡፡
‎
‎የዌብ ፖርታል ማበልጽጊያው የፓርቲያችንን ፖሊሲዎች ፣ እቅዶች ፣ ውሳኔዎች እና የልማት እንቅስቃሴዎች ለአባላቶቻችን ፣ ለጠቅላላው ህዝብ በግልጽነት እና በፍጥነት ተደራሽ ማድረግ ዓላማ አድርጎ የተዘጋጀ መሆኑንም ዋና ሀላፊው ገልጸዋል፡፡
‎
‎ የዜጎች እና የፓርቲው አባላት አስተያየት ፣ ጥያቄ እና ግብረ-መልስ በቀላሉ የሚሰበሰብበት ዲጂታል መድረክ መፍጠርም የዌብ ፖርታል ዓላማ መሆኑን ያስረዱት አቶ አብዱልፈታ የውስጥ አሰራርን በዲጂታል በማድረግ የአገልግሎት አሰጣጥን በማቀላጠፍና በማፋጠን ረገድም ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው ነው ብለዋል፡፡
‎
‎ አዲስ የዲጂታል ሚዲያ አማራጭ የፓርቲውን የመረጃ አያያዝ ከዘመኑ ጋር የሚያቀናጅ ነው ያሉት የሳንኩራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪና የዕለቱ የክብር እንግዳ ወ/ሮ ተሚማ ሙዴ በበኩላቸው የመረጃ አያያዝን ለማዘመን በዛሬው ዕለት የሚመረቀው ዌብ ፖርታል ፤ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግና የተቋሙን የመረጃ አያያዝ እንዲዘምን የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል ፡፡
‎
‎ዊብ ፖርታሉ የተቋሙን የውስጥ ስራዎች ከማቀላጠፍ ባሻገር የደህንነት ደረጃቸው የተጠበቁ መረጃዎችን ለረጅም ጊዜ በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲቀመጡ ማድረግ የሚያስችል ስለመሆኑም ወ/ሮ ተሚማ ገልፀዋል፡፡
‎
‎ተቋሙ የመረጃ አያያዝ በዘመናዊ መልኩ ለማደራጀትና የፓርቲውን ስራዎች በይፋ ተደራሽ ለማድረግ ያዘጋጀው የዌብ ፖርታል ወቅታዊና ተዓማኒ መረጃዎችን አባሉ በቀላሉ እንዲያገኝ የሚያደርግና የ"ዲጂታል ኢትዮጵያ" ጉዞ በተጨባጭ የታየበት መሆኑን ዋና አስተዳዳሪዋ ተናግረዋል፡፡
‎
‎በመድረኩ የዌብ ፖርታል አጠቃላይ ገጽታና አጠቃቀም እንዲሁም የተለያዩ መረጃዎችን እንዴት ማግኘት ይቻላል የሚለውን የዌብ ፖርታል ያበለፀገው የኢንቴል ሀብ ቴክኖሎጂ ባለቤት በሆነው መንሱር ሀምዛ በኩል በዝርዝር ቀርቧል፡፡
‎
‎በቀረበው ገለጻ አዲስ የዌብ ፖርታል በይነ-መረብ እንተርኔት ባለበት በማንኛውም ቦታና ጊዜ በቀላሉ በስልክም ሆነ በኮምፒውተር መጠቀም የሚቻል መሆኑ ተገልጿል፡፡
‎
‎ዌብ ፖርታሉ ፤ ዜናዎች ፣ መግለጫዎችን ፣ የፖሊሲ ሰነዶችንና ወቅታዊ መመሪያዎችን በአንድ ቋት አደራጅቶ ‎የያዘ ነው ተብሏል፡፡
‎
‎ ፖርታሉ አዳዲስ መረጃዎችንና ወቅታዊ ክዋኔዎችን ያለምንም የቴክኖሎጂ መወሳሰብ በፍጥነትና በቅፅበት እንዲጭኑ የሚያስችል ሲሆን በተመሳሳይ መልኩ አባላትና ደጋፊዎችም ያለምንም እንግልትና የጊዜ መራዘም የሚፈልጉትን መረጃ በስልካቸውም ሆነ በኮምፒውተራቸው በቀላሉ እንዲያገኙ ታስቦ የተሰራ ስለመሆኑን በመድረኩ ተመላክቷል።
‎
‎በመጨረሻም የዌብ ፖርታሉን ላበለፀገው የኢንቴል ሃብ ቴክኖሎጂስ ባለቤት ለወጣት መንሱር ሀምዛ የምስክር ወረቀት ተበርክቶለታል።